የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ሴት ሰራተኞች ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አከበሩ፡፡
መሪ ቃሉን "ሴቶችን እናብቃ፤ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ!" ያደረገውና ቁጥራቸው ከስድሳ በላይ የሆኑ ሴት የኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች የተካፈሉበት የጉብኝትና ውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡
ጉብኝቱ የተደረገው በአዳማ ፈትል ፋብሪካ ሲሆን ስራአስኪያጁ አቶ ደረጄና ባልደረቦቻቸው ለጎብኚዎቹ ስለድርጅታቸው የመጀመሪያ ደረጃ/የድርጅቱን አጠቃላይ ገፅታ አስመልክተው ገለፃ አድርገዋል፡፡
ስራአስኪያጁ አቶ ደረጄ እንዳሉት ተቋሙ አቶ ፈለቀ በቀለ እና ወ/ሮ መዓዛ አታላይ በተባሉ ባለሃብቶች በ2000 ዓ.ም የተቋቋመ የግል ድርጅት ሲሆን ሲመሰረት ክር በማምረት ሥራውን እንደጀመረና መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ጊዜ ጉዝ እና ሜዲካል ባንዴጆችን በማምረት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ጉዝ እና ባንዴጆችን በሀገር ውስጥ በማምረት ሀገርን ከተጨማሪ ወጪ ጭምር በመታደግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በመቀጠልም ጎብኚዎችን በሦስት ቡድን በመክፈል የፋብሪካውን የሥራ እንቅስቃሴ ከመጀመሪያ አስከ ፍፃሜ ያለውን ሂደት እንዲመለከቱ የተደረገ ሲሆን የጥጥ ምርትን ተረክቦና በተለያዩ ሂደቶች ውሰጥ እንዲያልፍ በማድረግ ጉዝ እና ሜዲካል ባንዴጅ እንዴት እንደሚመረት እያንዳንዱን ተግባር በማዘዋወር አስጎብኝተዋል፡፡ በተጨማሪም በምርት ሂደት የሚፈጠሩ ጠጣርና ፈሳሽ ተረፈ ምርቶች የሚታከሙበትን፣ ተመልሰው ወደሥራ የሚገቡበትንና የሚወገዱበት አግባብ ምን እንደሚመስል አስረድተዋል፡፡
አቶ ደረጄ አክለውም አሁን ባለው ተጨባጭ መረጃ በፋብሪካው ከሚሰሩት ሰራተኞች መካከል ከሰባ እስከ ሰማኒያ በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ስለመሆናቸውም ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜናም ይህንኑ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በአዳማ ደብሊው ኤል ኤክስፕረስ ሆቴል ወይይት ተደርጓል፡፡
በወይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ የኢንስቲትዩቱ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ዘነበች ማሞ እንደተናገሩት ሴት ልጅን ማብቃት ሀገርን ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረስ ነው፤ ይህንንም መርህ በአግባቡ በመረዳትና ወደተግባር በመቀየር ሀገራችንን እናሳድግ ያለንን ችሎታ እንረዳ ብለዋል፡፡
ከዳይሬክተሯ በማስከተል ሁለት ፕሮግራሞች የቀረቡ ሲሆን ሴቶች ቆራጦች በሆኑ ጊዜ ከስኬት ሊያቆማቸው የሚችል አንዳች ምድራዊ ኃይል አለመኖሩን በንፅፅርና ዓለም አቅፍ ጥናቶችን መሰረት በማደረግ ገለፃ ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ኮከቤ ለማ ቀጥለውም የዲሲፕሊንና ሥነ-ምግባር መርሆዎችን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ሴቶች ከዚህ አንፃር የተሻለ ማንነት የተላበሱ በመሆናቸው ምሳሌም አስተማሪም በመሆን ሀገራችሁንም ሆነ ተቋማችሁን ልትደግፉ ይገባል ብለዋል፡፡
በማስከተል የሰው ሀብት ልማት አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ሳሮን በለጠ በኢንስቲትዩቱ ሴቶች ፎረም ድጋሚ መቋቋም አስፈላጊነት ላይ ሰፋ ያለማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በቀጣይ ፎረሙን የሚመሩ ሰራተኞች ምርጫ ተካሂዷል፡፡