ኢንስቲትዩቱ በሁለት የጥናት ፕሮፖዛሎች ላይ ውይይት አካሄደ፡፡
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 02/2016 ዓ.ም (ኢስኢ) የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት በሳይንስ መሣሪያዎች ቴክኒክና ምህድስና ዳይሬክቶሬት ምርምር በተደረገባቸው ሁለት የጥናት ፕሮፖዛሎች ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡ የጥናት ፕሮፖዛሎቹ ‘Design and Prototype of Solar Direct Vaccine Refrigerator’ እና ‘Design and Prototype of Switch Mode Power Supply’ የተሰኙ ርዕሰ ጉዳዮችን የዳሰሱ ናቸው፡፡
የመጀመሪያውን የጥናት ፕሮፖዛል ያቀረቡት የሣይንስ መሣሪያዎች ቴክኒክና ምህንድስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንጂነር ትርፌሳ ፈይሳ እንደገለፁት በሀገራችን አብዛኞቹ ገጠራማ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ ባለመሆናቸው በመዳህኒት ማቀዝቀዣ ፍሪጅ እጦት ምክንያት ክትባቶችና መሰል መዳህኒቶች የቆይታ ጌዜአቸው የሚያጥርበት ሁኔታ አለ ፡፡ ጥናቱም ይህን ችግር ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በፀሀይ ሀይል የሚሰራ የመዳህኒት ማቀዝቀዣ ፍሪጅ በመስራት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ በማሰብ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ኢንጂነሩ ማብራሪያ ማሽኑ ከሚሰጠው ከፍተኛ ጥቅም ባሻገር በአነስተኛ ወጪ የሚገጣጠም እና የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ‘Design and Prototype of Switch Mode Power Supply’ የሚለውን ፕሮፖዛል ያቀረቡት በሣይንስ መሣሪያዎች ቴክኒክና ምህንድስና ዳይሬክቶሬት የልኬትና አናሊስስ ቡድን መሪ የሆኑት ኢንጂነር የማነ ተስፋዬ እንዳሉት በየትኛውም የስራ ቦታ ሆነ መኖሪያ ቤት ፓወር ሳፕላይ እንጠቀማለን፡፡ እንደሚታወቀው በሀገራችን የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ ድግግሞሽ ከፍተኛ በመሆኑ ብዙ ጊዜ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችና ከፍተኛ ማሽኖች በሚደርስባቸው ጉዳት ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ ስለሚሆኑ ጥናቱ ይህን ችግር በመቅረፍ ረገድ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
እንደ ቡድን መሪው ገለፃ ይህ ምርምር እቃው የሚጠቀመውን የኤሌክትሪክ መጠን /ዋት/ ፍጆታ ማመጣጠን ወይም መቆጣጠር ያስችላል፡፡ ኢንጂነሩ አክለውም ፓወር ሳፕላዩን በሀገር ውስጥ ምርት መተካትና የውጭ ምንዛሬን ማስቀረት ስለሚችል ጠቀሜታው ዘርፈብዙ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቀረቡት የጥናት ፕሮፖዛሎች ላይ ለአጥኝ ቡድኑ ጥያቄዎችና የማሻሻያ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን በቡድኑ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ተገኝተው የስራ አቅጣጫና ማጠቃለያ የሰጡት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ደርበው እንደተናገሩት ፕሮፖዛሉ እጅግ የሚደነቅና የሚበረታታ ነው፤ምርምሩን ላደረገው የጥናት ቡድንም ምስጋና ይገባል ብለዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ወደፊት የጥናት ማዕከል እንደሚሆን ስለሚጠበቅ መነሻ የሚሆኑ ጥናቶች መቅረባቸው በቀጣይ አቅማችንን አጠናክረን የተሻለ ሥራ እንደምንሰራ አመላካች ነው ሲሉ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
እንደዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ወጣቶች ከአንጋፋ ባለሙያዎች ልምድ መቅሠምና ራሳቸውን ማብቃት ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህ ምርምሮች ተጠናቅቀው ለውጤት እንዲበቁ ተቋሙ ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር በመሆን እገዛዎችን ያደርጋል፡፡ የጥናት ቡድኑም በትኩረት እንዲንቀሳቀስ አሳስበዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የኢንስቲትዩቱን ም/ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎችም ተሳትፈዋል፡፡