የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሠራተኞች የበዓል ስጦታ አበረከተ፡፡
አዲስ አበባ ጳጉሜ 4 ቀን 2016 ዓ.ም /ኢስኢ/ የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር በሰጡት አቅጣጫ መሰረት አዲስ ዓመትንና ጳጉሜ 4 "የህብር ቀን" ምክንያት በማድረግ አነስተኛ ገቢ ላላቸው አርባ ለሚሆኑ የተቋሙ ሠራተኞች ለበዓል መዋያ የሚሆን ዘይትና ዱቄት በስጦታ አበርክቷል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ደርበው እንደገለፁት ስጦታው በቂና ፍላጎታችሁን የሚያሟላ ነው ብለን ባናምንም መተሳሰባችንንና የአብሮነት ባህላችንን ለመግለፅ ብሎም እየከበደ የመጣውን የኑሮ ጫና ለመጋራት በማሰብ ያደረግነው ነው፡፡ አቅም ኖሮን ሁሉንም ሠራተኛ ማከተት ብንችል መልካም ነበር፤ነገር ግን ለጊዜው ይህን ማድረግ የሚያስችል አቅም ስለሌለን አነስተኛ ገቢ ካለቸው ሠራተኞች ለመጀመር ተገድደናል ብለዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ከዚህ ቀደም የተቋሙ የስራ አመራር አባላት ባሳለፉት ውሳኔ መሰረት የኢንስቲትዩቱ የሠራተኞች ካፍቴሪያ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሠራተኞች በግማሽ ዋጋ ቀንሶ አገልግሎት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው በቀጣይም በተለያዩ መንገዶች ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የሠላም፣የጤና፣በጋራ ተባብረን ውጤት የምናስመዘግብበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የኢንስቲትዩቱን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቅረአብ ማርቆስን ጨምሮ የማናጅመንት አባላት ተገኝዋል፡፡
በዕለቱ የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ማናጅመንት አባላት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን በመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የጎበኙ ሲሆን ከ7 ሺህ 5 መቶ በላይ ለሚሆኑ የማዕከሉ ተረጅዎች ማዕድ ማጋራትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ9.5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፎችን በማድረግ አክብረው ውለዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚንስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌም ድጋፉ ቀጣይነት እንደሚኖረው ቃል የገቡ ሲሆን የድርጅቱ መስራች የክብር ዶክተር ቢኒያም በለጠ ለተደረገላቸው ድጋፍና አብሮነት ምስጋና አቅርበዋል፡፡