አራቱ የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት ያዘጋጁት የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ተካሄደ፡፡
ግንዛቤ ማስጨበጫውን በንግግር የከፈቱት የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ መዓዛ አበራ እንደተናገሩት የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት በአንድ የተሳተፉበት ፕሮግራም መዘጋጀቱ ሕብረተሰቡም ሆነ ደንበኞች የየተቋማቱን ኃላፊነትና ተግባር ልዩነት እንዲገነዘቡ እንዲሁም የትኞቹ ቦታዎች ላይ ደግሞ ተቋማቱ በጋራ እንደሚሰሩ መረጃ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ተሳታፊዎች ለሚኖራቸው ሃሳብና ጥያቄ ከምንጩ ምላሽ የሚያገኙበትን ሁኔታም ያመቻቻል ብለዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ጨምርው እንዳሉት የጥራት ደረጃን ከፍ የማድረግ ፍላጎት ያለው መንግስት እስከ አስራ ሁለት የሚደርሱ ግዙፍ የሕንፃ ግንባታዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረው በዚህም ከፍተኛ የአገልግሎት ጥራትና ስፋት ለውጥ እንደሚኖር አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከመክፈቻ ንግግሩ በማስቀጠል የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማቱ ተወካዮች ስለሚሰጧቸው አገልግሎቶችና ደረጃዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የአንድ ተጋባዥ ተቋም የሥራ ኃላፊም በምግብ ምንነትና ደህንነት ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል፡፡
የኢትጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩትን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የሣይንሳዊ ሥነ-ልክ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ጌርጊሶ እንደገለጹት ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት በካሊበሬሽን ዘርፍ ከስድስት በላይ ዓለማቀፍ እውቅና ያለውና በሌሎችም ዘርፎች ተጨማሪ እውቅና ለማግኘት እየሰራ ነው፡፡ በሣይን መሳሪያ ዘርፎችም በማማከር፣በሥልጠና፣በቴክኒክና ጥገና ዙሪያ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ጨምረው እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ በሌሎች ሀገሮች እንደሚሰራበት የጥናትና ምርምር ተግባራት ላይ በማተኮር አገልግሎቶችን ብቁ ለሆኑ ግለሰቦችና ድርጅቶች የማስተላለፍ ዕቅድ ያለው ሲሆን ይህንንም ለማሳካት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የድርጅቶች ተወካዮችም በቀረቡት ሃሳቦችና በጥራት መሰረተልማት ተቋማት አገልግሎትና እንቅስቃሴ ዙሪያ ጥያቄ አቅርበው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡