የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ለኢፌዲሪ አየር ሀይል ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና አጠናቀቀ፡፡
አዲስ አበባ፡ ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም (ኢሥኢ) የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ቢሾፍቱ ለሚገኘው የኢፌዲሪ አየር ሀይል ወታደራዊ መኮንኖች ለተከታታይ ሦስት ሳምንታት ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና አጠናቅቋል፡፡
አየር ሀይሉ ያቀረበውን የስልጠና ፍላጎት ጥያቄ ኢንስቲትዩቱ በሙሉ ፈቃደኝነት ተቀብሎ በክብደት/Mass/፣ በግፊት/Pressure/፣ በሀይል/Force/ እና በኤሌክትሪካል ሥነ-ልክ/Electrical Metrology / እንዲሁም በ ISO/IEC17025/2017 ርዕሶች ላይ ትኩረት አድርጎ 13 ለሚሆኑ ወታደራዊ መኮንኖች ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ማጠናቀቂያ መርሀ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ደርበው እንዳሉት የሀገር ጋሻና መከታ ለሆነው የኢትዮጵያ አየር ሀይል ወታደራዊ መኮንኖች ስልጠና መስጠት በመቻላችን ኩራትና ደስታ ተሰምቶናል፡፡ ጥያቄ ሲቀርብልን በደስታ በመቀበልና ቀድመን የስልጠና ፍላጎት ጥናት በማድረግ የተሻለ ስልጠና ለመስጠት ጥረት ተደርጓል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የእኛ ሰርቶ መግባትና መኖር በእናንተ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ስልጠናው ቢያንስ እንጅ አይበዛም ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር ሙሉጌታ ገለፃ ከዚህ ቀደም እድሉን አግኝተው በዚህ ታላቅ ተቋም በካሊብሬሽን ስራ ተመድበው ለስድስት ወር መስራታቸውን አስታውሰው ካከናወኑት ተግባር በበለጠ ወታደራዊ ስነ-ስርዓትን፣ የስራ ፍቅርን፣ሁሌም ዝግጁ መሆንን በአጠቃላይ የህይወት መመሪያን የተማሩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ከዚህ በኋላም ከአየር ሀይሉ ጋር በተሻለ ቁርጠኝነትና ዝግጅት በጋር እንደሚሰሩ ቃል የገቡ ሲሆን ስልጠናውን ለሰጡ የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢፌዲሪ አየር ሀይል ምክትል አዛዥና የሎጀስቲክ መመሪያ ኃላፊ ብርጋዴር ጄነራል ነገራ ሌሲሳ ለወታደራዊ መኮንኖች የስልጠና የምስክር ወረቀት ሲሰጡ እንደተናገሩት የኢፌዲሪ አየር ሀይል ከተቋቋመበት 1921 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ዝቅታዎችንና ከፍታዎችን እያለፈ አሁን ላለበት ከፍተኛ ደረጃ መድረስ ችሏል ብለዋል፡፡
እንደ ምክትል አዛዡ ገለፃ ለታላቅ ሀገር ታላቅ አየር ሀይል በሚል መርህ በተለይም ከለውጡ ወዲህ የተደራጀና ብቁ የሰው ሀይል ማፍራት፣ ጊዜው የሚጠይቀውን ዘመናዊ ትጥቅ መታጠቅ እንዲሁም መሰረተ ልማትን ለማሳደግና አካባቢን ለመለወጥ በተከናወነው ጠንካራ የሪፎርም ስራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡
ዘመናዊና ረቂቅ መሳሪያዎችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል፣ የላብራቶሪ አቅማችንን ለማዘመንና የትጥቅ ሀይሉን ለማጠናከር ደግሞ ብቁ የሰው ሀይል አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም ያሉት ብርጋዴር ጄነራሉ ይህን በመገንዘብ የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት በፈቃደኝነት ብቁ ባለሙያዎችን በመመደብ ለሰጠው የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ምክትል አዛዡ በመጨረሻም ለኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ሰርተፊኬትና የኢፌዴሪ አየር ሀይል ዓርማን በስጦታ ያበረከቱ ሲሆን በቀጣይም የሁለቱንም ተቋማት የጋራ አቅም በመጠቀምና ውጤታማ ስራ በመስራት የሀገር አለኝታነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልፀው ስልጠናውን የወሰዱ ወታደራዊ መኮንኖችም ተግባር ላይ በማዋል አሰራሩን ከዚህ በለጠ ማዘመን እንደሚገባ አሳስባለሁ ሲሉ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቅረአብ ማርቆስን ጨምሮ ሌሎች የተቋሙ አመራሮችና አሰልጣኞች የአየር ሀይሉን ቅጥር ግቢና ወርክሾፖች ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን ባዩት ነገር መደመማቸውንና ከሀገር አልፎ የአፍሪካ ኩራት መሆኑንና ለታላቅ ሀገር ታላቅ አየር ሀይል የሚለውን መፈክር በተግባር ያረጋገጥንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ራስን አዘምኖ ሀገርን ከማንኛውም ጠላት መጠበቅ ታላቅ ተግባር ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ተቋሙ የሰው ሀይልን ለማብቃት በሰጠው ትኩረት ዘመናዊ አየር ሀይል መገንባቱን ተመልክተናል ካሉ በኋላ ለተደረገላቸው በፍቅር የተሞላ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡