ኢንስቲትዩቱ የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት ሪፖርት ገመገመ፡፡
አዲስ አበባ፡ መስከረም 27/2018 ዓ.ም (ኢሥኢ)
የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት በ2018 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት የተከናወኑ ተግባራትን አፈፀፃም በዛሬው ዕለት ገምግሟል፡፡ ሪፖርቱን ያቀረቡት በኢንስቲትዩቱ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ስንታየሁ ወንድሙ የኢንስቲትዩቱን የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ፣ የሦስተኛ ዓመት የመካከለኛ ዘመን የልማት ዕቅድ መነሻ በማድረግ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን ገልፀዋል፡፡ የደንበኛ/የባለድርሻ እርካታን፣ ተደራሽነትን፣ የበጀት አጠቃቀም ውጤታማነትን ከማሳደግ፣ በዓለም አቀፍ የሥነ-ልክ ድርጅት (BIPM-KCDB) ማስመዝገብ፣ የአሰራር ቅልጥፍናን፣ ቅንጅታዊ አሰራርን ከማሻሻል፣ የሰው ሀይልን ከማሟላት አኳያ በዚህ ሩብ ዓመት ውጤታማ ስራ መከናወኑን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ሙሉጌታ ደርበው /ዶክተር/ በበኩላቸው እንደገለፁት የዘንድሮውን የሩብ ዓመት ግምገማ ልዩ የሚያደርገው መንግስት የገንዘብ እጥረት ቢኖርበትም የመንግስት ሠራተኛው ያለበትን የኑሮ ጫና ተቋቁሞ ህዝብንና መንግስትን በታማኝነት ማገልገል መቻሉን በመገንዘብ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ጫናውን የሚያቀል ድጎማ ባደረገበት ማግስት መካሄዱ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ባሳለፍነው አንደኛ ሩብ ዓመት ፈርጀ ብዙ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን ለአብነት የተወሰዱብንን ዕውቅናዎች ያስመለስንበት፣ የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንት ኤክስፖንና ከዚሁ ጎን ለጎን ሁለት የፓናል ውይቶችን በስኬት ያካሄድንበት፣ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቅ የነበረውን የአዳራሽ ወንበር በአነስተኛ ዋጋ ያሟላንበት፣ የተለያዩ ስልጠናዎችን የሰጠንበት፣ የካሊብሬሽን ስራዎችን በስፋት ያከናወንበት፣ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ምስጉን ሠራተኞች ዕውቅና የሰጠንበት፣የተመራማሪዎችን ጥቅማጥቅም ሠነድ ዝግጅት ለማፀደቅ ብዙ ርቀት የሄድንበት እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሠራተኞች ማዕድ የማጋራት በጎ ተግባር ያከናወንበት ስኬታማ ሩብ ዓመት እንደነበር አውስተዋል፡፡
በያዝነው በጀት ዓመት የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ እጅና ጓንት በመሆን በትብብርና በአንድነት ከመደበኛ የስራ ሠዓት በተጨማሪ የዕረፍት ቀናትን ጭምር በመስራት ባደረጉት ብርቱ ጥረት ምክንያት የሚጨበጥ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል፤ ለዚህም ምስጋና ይገባል፡፡ ይህን የስራ ተነሳሽነትና የትብብር መንፈስ በማጠናከር በተለይ ደግሞ ስራን ከመልካም ሥነ-ምግባር ጋር በማጣመር የራሳችንን ክብር ብሎም የተቋሙን በጎ ስም አጠናክሮ ማስቀጠል ከሁሉም ይጠበቃል ሲሉ ዶክተር ሙሉጌታ አክለው ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ለዋና ዋና ተግባራት ትኩረት ስጥቶ ከመስራት ባሻገር በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ኢንስቲትዩቱን ወደ ኢንተርፕራይዝ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት መደገፍ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቅርአብ ማርቆስ እንደተናገሩት ተቋሙ እየሰፋ ስለሆነ ይህን የሚመጥን የተሟላና ብቁ ሰው ሀይል ማሟላት፣ አሰራርን ማዘመን፣ ተደራሽነትን ማስፋት ከእያንዳንደችን ሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ የተቋሙን ድህረገፅ በማዘመን ረገድ አበረታች ስራ የተሰራ ቢሆንም በወቅታዊ መረጃዎችና በፈጠራ ስራዎች ማጎልበት ስለሚያስፈልግ የስራ ክፍል ኃላፊዎች ተገቢውን መረጃ በመስጠት መተባበር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
ዝቅተኛ አፈፃፀም የታየባቸውን ተግባራት ትኩረት ሰጥቶ በመፈፀም በሁለተኛው ሩብ ዓመት ስንገናኝ ከዚህ የበለጠ ውጤት ይዘን መቅረብ ይኖርብናል ሲሉም በአፅንኦት አስገንዝበዋል፡፡
በመጨረሻም የውይይቱ ተሳታፊዎች መንግስት ያለብንን የኑሮ ጫና ተመልክቶ ላደረገው ድጎማ አመስግነው ሥራን ከጥቅም ጋር ሳናቆራኝ በተሰማራንበት የስራ ዘርፍ ውጤት ለማስመዝገብና ህዝብን ለማገልገል ብሎም መንግስተ የጣለብንን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡