የዋና ዳይሬክተሩ መልዕክት
የአለም የስነ-ልክ ቀን እ.ኤ.አ በግንቦት 20 ቀን 1875 በአስራ ሰባት ሀገራት ተወካዮች የተፈረመው የሜትር ስምምነት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚታወስበት ዓመታዊ በዓል ነው። እ.ኤ.አ በመስከረም 2023 በወጣ ሪፖርት መሰረት አባል አገራት 64 የደረሱ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ 33 አገራት ደግሞ ተባባሪ አባል ናቸው። ስምምነቱ ዓለማችን ሳይንሳዊ መሰረት ያለው፣ ተናባቢ፣ ተሳሳሪ እና ተመሳሳይ አሃድ መጠቀም እንድትችል እድሉን የከፈተ እና ለኢንዱስትሪ፣ ለንግድ እና ለማህበረሰብ ልማት አለም አቀፍ የትብብር ማዕቀፍ መሰረት የጣለ ነው። የስምምነቱ ዓላማ ዛሬም ድረስ የ 1875ቱን ያክል የዓለማችን አስፈላጊ አጀንዳ በመሆን የቀጠለ ነው።
ኢንስቲትዩታችንም ለሀገራችን ብልጽግና የሚኖረውን አበርክቶት ለማሳደግ፣ አገልግሎቶቻችንን ለማሻሻል፣ የአሰራር ክህሎታችንን እና ብቃታችንን ለመገንባት ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት እድል ይፈጥርልን ዘንድ በርካታ ጥረቶች በማድረግ የሥነ-ልክ ቀንንን በየዓመቱ እያከበረ ይገኛል። አንስታይን “በምትናፍቃት ቆንጆ ኮረዳ እቅፍ ውስጥ ለአንድ ሰዓት ስታሳልፍ ደቂቃም የቆየህ አይመስልህም፤ በጋለ ምዳጃ ላይ ለአንድ ደቂቃ እንድትቀመጥ ብትደረግ ግን ለአንድ ሰዓት የቆየህ ይመስልሃል” ብሏል ተብሎ ለዘመናት እንደሚታወሰው። ስራችን ገብቶን ስንሰራ ይቀለናል፤ ያስደስተናል፤ አይደከመንም። በስራችን ላይ እና ለስራችን የሚጠቅም ክህሎት ገንቢ አማራጮች ላይ የምናውለው የግዜ መጠን ለስራችን ሳይንሳዊ መሰረቶች እና እስትራቴጂያዊ ስኬቶች ያለንን የመረዳት መጠን መለኪያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የሥነ-ልክ ቀንን ምክንያት በማድረግ የኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች፣ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች፤ በሥነ- ምግባራቸውና ቅን ልቡናቸው፣ በጹሁፎቻቸውና በውጤታማ አፈጻጸማቸው እውቅና ይሰጣቸዋል፤ ይሸለማሉ፤ ይበረታታሉ። እንደ አንድ የተቋሙ ማህበረሰብ በዓሉን በሀገራችን የቤተሰብ ዓውድ ዓመት ስርዓት መሰረት ማእድ እየተጋራንና እየተጨዋወትን እንድናሳልፍም የበዓል ዝግጅት ተደርጓል።
በዚህም የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች ጠቀሚ ምርምሮች እንዲያደርጉ፣ ልምዶቻቸውን ቀምረው እንዲያካፍሉ፣ እንዲጽፉ እና በተለያዩ የህትመት አማራጮች ስራዎቻቸውን ተደራሽ እንዲያደርጉ ይበረታታሉ። ይህም በመሆኑ ዛሬ ላይ ሆነው ለአሁኑ ዓመት ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ሁለት ሶስት ዓመታት በብዓሉ እውቅናን የመቸር፣ የመከበር እና የመሸለም በረከቶችን ለማጣጣም ባለሙያዎቻችን እና ተመራማሪዎቻችን አስቀድመው ዘግጅት የማድረግ ጅማሮች እያሳዩን ነው። ይህ እንዲቀጥል እንተጋለን።
“የሰው አገሩ ምግባሩ የከብት አገሩ ሳሩ” በሚለው ምሳሌያዊ መዘክራችን እንደተገለጸው፤ የምንሰራው የሳሩን መጠን ታሳቢ አድረገን ሳይሆን ሰው የመሆን ክብርን በሚያጎናጽፈን የአገር ፍቅር እና ሃላፊነትን በታማኝነት የመወጣት ስሜት መሆን ይኖርበታል። ሌላኛው እውነት ኢንስቲትዩታችንን በብቃት ለማገልገል ጥረት በምናደርገው ልክ ዓለም ዓቀፍ ባለሙያ የመሆን እድል ይፈጥርልናል። ስለሆነም ተቋማችን የኛ የእያንዳንዳችን ጸጋ፣ የእያንዳንዳችን ቤት እንደሆነ መረዳት ይኖርብናል። ይህን ከተረዳን ሰው ለቤቱ እንዴት እንደሚሰራ ነጋሪ አያስፈልገውም እና አስተሳሰቡ ሃላፊነታችንን በውጤታማነት እና በታማኝነት ለመወጣት ተጨማሪ አቅም ይፈጥርልናል።
ሙሉጌታ ደርበው (ዶ/ር)
የኢትዮጵያ ሥነልክ ኢንስቲትዩት
ዋና ዳይሬክተር