የጥራት መንድር አመራርና ሠራተኞች 18ኛውን የሠንደቅ ዓላማ ቀን አከበሩ፡፡
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (ኢሥኢ)
የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩትን ጨምሮ የጥራት መንደር የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በተገኙበት በውቡ የጥራት መንደር ቅጥር ግቢ ውስጥ "ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብስራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ!" በሚል መሪ ቃል 18ኛውን የሠንደቅ ዓላማ ቀን በዓል አክብረዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ በመገኘትና የጥራት መንደርን በመወከል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦንሳ ባይሳ እንዳሉት የዘንድሮው የሠንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ ሀገራዊ ድሎች ታጅቦ የሚከበርና የኢትዮጵያ ኩራት በሆነው የጥራት መንደር ግቢ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ ያከበርንበት ዓመት በመሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ቦንሳ ገለፃ በብዙ ጫና እና ተፅዕኖ ውስጥ ሆነን በራሳችን ሀብትና ላብ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ብሎም ከግደቡ ባልተናነሰ መልኩ ወሳኝ የሆነውን የጋዝ ፕሮጀክት ያስመረቅንበትና ሌሎች በርካታ ድሎችን ያስመዘገብንበት ጊዜ ላይ በመሆናችን ሠንደቅ ዓላማችንን በፍጹም ደስታና ኩራት ከፍ እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም የዚህ ግቢ አመራርና ሠራተኞች በተመዘገቡ ድሎች ሳንዘናጋ በተሰማራንበት የስራ ዘርፍ ውጤት በማስመዝገብ ለበለጡ ድሎች መዘጋጀት፣ የሀገራችንን እና የሠንደቃችንን ከፍታ በዓለም ለማጉላት መሽቀዳደም ይኖርብናል ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል፡፡
በጨረሻም ሁሉም የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርን በመዘመርና ሠንደቅ ዓላማ በመስቀል በዓሉን አጠናቀዋል፡፡