themes/custom/conbiz የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ሠራተኞች የዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሄዱ፡፡ | EMI Skip to main content
emi

የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ሠራተኞች የዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሄዱ፡፡

የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሠራተኞች የተቋሙን የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ አካሂደዋል፡፡

ሪፖርቱን ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ የዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ስንታየሁ ወንድሙ እንዳብራሩት የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ከ2016-2018 የኢንስቲትዩቱን ስትራቴጂክ ዕቅድ መሰረት በማድረግ፣ በ2015 በጀት ዓመት ያልተጠናቀቁ ተግባራትን በማካተት የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወራት አፈጻጸም በመገምገም ዕቅዱ ተከልሶ ወደ ትግበራ መገባቱን ገልፀው በ2016 በጀት ዓመት በ9 ወሩ የተከናወኑ ዋና ዋና የተግባራት አፈጻጸም በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በዚሁ መሰረት ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም፣ የሀብት አጠቃቀም እና የአገልግሎት አሰጣጥ ስራዎች፣ በቁልፍ የውጤት አመላካቾች ላይ የተመሰረተ የልማት ዕቅድ አፈጻጸም ትንተና እንዲሁም በአፈጻጸም ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች የሚሉ ጉዳዮች በሪፖርቱ ተመላክተዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ በበጀት ዓመቱ ከዓለም አቀፍ ሥነ-ልክ ስርዓት ጋር የተጣጣመ የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ስርዓትን ለመዘርጋትና ተግባራዊ ለማድረግ ወንድ 141 ሴት 94 በድምሩ 235 ሠራተኞችን ይዞ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ በተጠናከረ መልኩ ለማከናወን ጥረት ሲደደረግ ቆይቷል ብለዋል፡፡ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ፣ የደንበኛ እርካታ፣ ተደራሽነትን ከማሳደግ፣ እንዲሁም የአሰራር ቅልጥፍናን ከማሻሻል፣ የሰራተኛውን ብቃት ከማሳደግ አኳያ ብሎም ሴክተር ዘለል ተግባራትን በሚመለከት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በግምገማው ላይ የተገኙት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ደርበው እንደተናገሩት በዘጠኝ ወሩ ተቋሙ የያዘውን ተልዕኮ ለማሳካት ከፍተኛ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በተለይ ጥራትና ምርታማነትን የሚጨምር ስራ ለመስራት ብቃት ያለው የሰው ሀይል ማፍራት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

እንደዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ በበጀት ዓመቱ በርከት ያሉ ጠንካራ ጎኖች ቢኖሩም ስራን የማንጠባጠብ፣ የቅንጅታዊ አሰራር መላላት፣ የመረጃ አያያዝና መሰል ችግሮች መስተዋላቸውን ጠቅሰው በቀሪዎቹ ሦስት ወራት ተቋሙን ውጤታማ ለማድረግ መልካም ሰብዕናን በመላበስ፣ ክህሎትን በመገንባትና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጎልበት ጥንካሬዎችን የበለጠ ማጎልበት ችግሮችን ደግሞ በማስተካከልና ውጤታማ ስራ በመስራት የተቋሙን ተልዕኮ ማሳካት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሪፖርቱ አፈፃፀማችንን በሚገባ የዳሰሰ በመሆኑ ጥንካሬያችንና ድክመቶቻችንን የተገነዘብንበት ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ወራት ያሉብንን ድክመቶች በማረምና በጋራ ተባብረን በመስራት የተቋሙን ተልዕኮ ዳር ለማድረስ እንተጋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከሪፖርቱ ባሻገር በኢንስቲትዩቱ የካሊብሬሽን አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የተዘጋጀ የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡