themes/custom/conbiz የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ሠራተኞች 13ኛውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምስረታ በዓል አከበሩ፡፡ | EMI Skip to main content
GRED

የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ሠራተኞች 13ኛውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምስረታ በዓል አከበሩ፡፡

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27/2016 ዓ.ም (ኢስኢ) የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሠራተኞች በህብረት ችለናል! በሚል መሪ ቃል 13ኛውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምስረታ በዓል በፓናል ውይይት አክብረዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ደርበው እንዳሉት የግድቡ ምስረታ ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮ መላው የሀገራችን ህዝብ በአንድነት በመቆም በእውቀት፣ በጉልበት፣ በገንዘብና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ በንቃት በመሳተፍ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ የኢንስቲትዩቱ አመራችና ሠራተኞችም የተላለፈውን ሀገራዊ ጥሪ በድስታ በመቀበል ቦንድ በመግዛትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ የሚጠይቀውን ሙያዊ ድጋፍ በብቃት በመወጣታችሁ እንዲሁም ቦታው ድረስ ሄዳችሁ በመጎብኘታችሁ ምስጋና ይገባችኋል፤ በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ይህን መልካም ተግባር አጠናክራችሁ እንደምትቀጥሉ እተማመናለሁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ዶክተር ሙሉጌታ አያይዘውም በግድቡ ግንባታ ላይ ያሳያችሁትን ርብርብ በተሰማራችሁበት የሥራ ዘርፍም በመድገም ተቋሙን ወደፊት ማራመድ ይጠበቅባችኋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የመወያያ ሰነዱን ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቅረአብ ማርቆስ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሀገራችን ህዝብ የጋራ ክንድ የግንባታው ጠቅላላ አፈፃፀም 95 በመቶ መድረስ ችሏል፡፡ የህዳሴ ግድብ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ህዛባዊ ተሳትፎው በከፍተኛ ግለት ተቀጣጥሎ ላለፉት 13 ዓመታት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ የህዳሴ ግድቡ እዚህ ለመድረስ ከቅድመ አባይ ታሪክ ጀምሮ የኢትዮጵያ መሪዎች በዓለምም ሆነ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ያጋጠሟቸውን በርካታ ፈተናዎች ባደረጉት ብርቱ ተጋድሎና ቅብብሎሽ የነበራቸው ዕቅድ በእኛ ዘመን በመሳካቱ ከፍተኛ ኩራት ይሰማናል ብለዋል፡፡

አቶ ፍቅረአብ አክለውም ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የዘረዘሩ ሲሆን ፍፃሜውን ለማየትና ደስታችንን ሙሉ ለማድረግ የቀደመ ተሳትፏችንን አጠናክረን ማስቀጠል ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ታላቁ የህዳሴ ግድብ አንድነት ምን ያህል ጉልበት እንዳለው ያየንበት፣ ፖለቲካና ሀገርን የለየንበት ብሎም ታላቅ ድል ያስመዘገብንበት ፕሮጀክት ነው፡፡ ለግድቡ ስኬት እንደ መላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እኛ የተቋሙ ሠራተኞችም ቦንድ በመግዛት፣ ሙያዊ እገዛ ወይም የካሊብሬሽን አገልግሎት በመስጠት አመርቂ ስራ በመስራታችን ምክንያት ከማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ምስጋና ተችሮናል ብለዋል፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለፃ ግድቡ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ የሀገር ተልዕኮ ፈፃሚዎችም ሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች በዲፕሎማሲው ዘርፍ ላደረጉት ቆራጥ ትግል እንዲሁም ላበረከቱት ማንኛውም ዓይነት ድጋፍ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ከሚሰጠው ጠቃሜታ ባሻገር የእውቀት ሽግግር ያደረግንበት፤ ለወደፊት በራሳችን የሰው ሀይል እና ገንዘብ ተጨማሪ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መስራት እንደምንችል የተገነዘብንበት በመሆኑ ደስታ ይሰማናል ያሉት ተወያዮቹ ወደፊትም ግደቡ በድል እስኪጠናቀቅ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ ነን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም በፌዴራል መንግስት መ/ቤቶች መዋቅራዊ አደረጃጀት ለውጥ መሰረት የመንግስት ሠራተኞች ድልድል አፈፃፀም መመሪ ዙሪያ ከኢፌዴሪ ሲሰቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመጡ ባለሙያ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ኢንስቲትዩቱ እያከናወነ ባለው መዋቅራዊ አደረጃጀት ለውጥ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፤ድልድሉም በአጭር ጊዜ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡