Skip to main content
emi

የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት አመራርና ሠራተኞች የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሄዱ፡፡

አዲስ አበባ፡ መጋቢት፡ 29/2017 ዓ.ም (ኢሥኢ) የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት አመራርና ሠራተኞች መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም የተቋሙን የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዋና ዋና የተግባራት አፈፃፀምን ገምግመዋል፡፡

ሪፖርቱን ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ስንታየሁ ወንድሙ እንዳብራሩት የኢንስቲትዩቱን የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሰረት በማድረግ፣ በ2017 በጀት ዓመት በ9 ወሩ የተከናወኑ ዋና ዋና የተግባራት አፈጻጸምን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በዚሁ መሰረት ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም፣ የሀብት አጠቃቀም እና የአገልግሎት አሰጣጥ ስራዎች፣ በቁልፍ የውጤት አመላካቾች ላይ የተመሰረተ የልማት ዕቅድ አፈጻጸም ትንተና እንዲሁም በአፈጻጸም ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች የሚሉ ጉዳዮች በሪፖርቱ ተመላክተዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ በበጀት ዓመቱ ከዓለም አቀፍ ሥነ-ልክ ስርዓት ጋር የተጣጣመ የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ስርዓትን ለመዘርጋትና ተግባራዊ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ፣ የደንበኛ እርካታ፣ ተደራሽነትን ከማሳደግ፣ እንዲሁም የአሰራር ቅልጥፍናን ከማሻሻል፣ የሰራተኛውን ብቃት ከማሳደግ አኳያ ብሎም ሴክተር ዘለል ተግባራትን በሚመለከት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመው የተቋሙ አጠቃላይ አፈፃፀም በአማካይ 91 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን ገልፀዋል፡፡

በግምገማው ላይ የተገኙት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ደርበው እንደተናገሩት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ዕቃ በማጓጓዝና በማደራጀት ስራ ላይ ተጠምደን የቆየን ቢሆንም ጎን ለጎን የአገልግሎት ስራችንን ሳንረሳ በመከወናችን በዘጠኝ ወሩ ተቋሙ የተሻለ አፈፃፀም እንዲያስመዘገብ ማድረግ ብሎም ኢንስቲትዩቱ የያዘውን ተልዕኮ ለማሳካት ከፍተኛ ርብርብ መደረጉን ገልፀው በተለይ ጥራትና ምርታማነትን የሚጨምር ስራ ለመስራት ብቃት ያለው የሰው ሀይል ማፍራት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

እንደዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ በበጀት ዓመቱ በርከት ያሉ ጠንካራ ጎኖች መመዝገባቸውንና በንፅፅር የተሻለ አፈፃፀም አሳይተዋል ያሏቸውን የሥራ ክፍሎችን በመጥቀስ ጭምር አመስግነዋል፡፡ ይሁንና ተግባራትን ያለምንም እንከን ተወጥተናል ማለት አይደለም ያሉት ዶ/ር ሙሉጌታ ስራን የማንጠባጠብ፣ የቅንጅታዊ አሰራር መላላት፣ የመረጃ አያያዝና መሰል ችግሮች አሁንም መኖራቸውን ጠቅሰው በቀሪዎቹ ሦስት ወራት ተቋሙን ውጤታማ ለማድረግ መልካም ሰብዕናን በመላበስ፣ ክህሎትን በመገንባትና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጎልበት ጥንካሬዎችን የበለጠ በማስፋት ችግሮችን ደግሞ በማስተካከልና ውጤታማ ስራ በመስራት የተቋሙን ተልዕኮ የተሟላ ማድረግ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሪፖርቱ አፈፃፀማችንን በሚገባ የዳሰሰ በመሆኑ ጥንካሬያችንና ድክመቶቻችንን የተገነዘብንበት ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ወራት ያሉብንን ድክመቶች በማረምና በጋራ ተባብረን በመስራት የተቋሙን ተልዕኮ ዳር ለማድረስ እንተጋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከሪፖርቱ ባሻገር በሥነምግባር ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ስልጠና የሰጡት ኢንስቲትዩቱ የሥነ-ምግባርና መከታተያ ሥራ-አስፈፃሚ አቶ አሰፋ ተስፋዬ የሥነምግባርን አጠቃላይ ገጽታና መገለጫዎቹን፣ ለሥነ-ምግባር ችግር ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን፣ ሥነ-ምግባራዊ አጣብቂኝ ምን እንደሚመስልና ሰራተኞች ከዚህ አንፃር የሥነምግባርን ጉዳይ እንዴት መመርመር፣ መረዳትና መከተል እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ለውይይት የሚሆኑ ሃሳቦችን አቅርበው ሰራተኞች በሰፊው ተነጋግረውበታል፡፡