themes/custom/conbiz የሳይንስ መሳሪያዎች ስልጠናና ምክር ዳይሬክቶሬት በአናሎግና ድጂታል ኤሌክትሮኒክስ ዙሪያ ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡ | EMI Skip to main content
Trainees on job training

የሳይንስ መሳሪያዎች ስልጠናና ምክር ዳይሬክቶሬት በአናሎግና ድጂታል ኤሌክትሮኒክስ ዙሪያ ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡

ስልጠናውን ብንግግር የከፈቱት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ደርበው እነኳን እንድትገለገሉበት በሚያስፈልጋችሁ ቴክኖሎጂ እየገገነባነው ወዳለው የጋራ ኢንስቲትዩታችን በደህና መጣችሁ። ስልጠናውን ስናዘጋጅ በበቂ ምክክር በመሆኑ ለስራችሁና ለቀጣይ ስልጠናዎች መሰረት ይጥላል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።

በተለይ የሚከፈለንን ክፍያ ለምንሰራው ስራ ማነፃፃሪያ ሳናደርግ፤ አጃችን ላይ ያለውን የማገልገል እድል በተቋሞቻችን የተደረራጁ ቴክኖሎጂዎችን እና የመንግስት የስራ ሰዓትን በውጤታማነትና በቅልጥፍና መጠቀም ላይ ማተኮር አለብን፡፡ በመንግስት ቤት ስንሰራ ትልቁ ቱርፋታችን ህዝባችንና ሀገራችንን ማገልገል ሲሆን በዚሁ እየረካን፤ በምናገኛቸው የስልጠናና የትምህርት እድሎች እራሳችንን በእውቀትና በክህሎት ማብቃት እንደሆነ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል ሲሉ አስረድተዋል።

ስልጠናው በየጤና ተቋማቱ የህክምና መሳሪዎች እያሉ ባልተገባ የጥገና ውስንነት የሚስተጓጎል የህክምና ሂደት እንዳይኖር የሚፈለገውን ክህሎት ሳይቆራረጥ በጋራ ለመገንባት መሰረት ይጥላል ብለን እናስባለን። ይህ ግንኙነታችን የጤናው ዘርፍ ሴክተር መስሪያ ቤቶችና የስነ-ልክ ኢንስቲትዩት በሀገራችን የህክምና መሳሪዎችን የአጠቃቀም ውጤታማነትንና ዘመናዊነትን ለማረጋገጥ ተቀራርበን እና ተቀናጅተን የምንሰረበትን ምእራፍ እንደ አዲስ የምንከፍትበት ይሆናል። በስልጠናው የምትሹትን የምታሳኩበት፣ ሰልጣኞች ከአሰልጣኞች እና ሰልጣኞች እርስ በእርሳችሁ የሙያ ወንድማማችነት የምታፈሩበት እንዲሆን እንመኛለን ሲሉ ገልፀዋል።

ለዚህ ስኬት አብረውን ለሰሩት የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ስልጠናው እንዲሳካ ጥልቅ እና ሙያዊ ጥረት ያደረገውን በኢንስቲትዩታችን የሳይንስ መሳሪያዎች ስልጠናና ምክር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢነጂነር አበባየሁ ማሞንና የዳይሬክቶሬቱን ባለሙዎች በሙሉ ከልብ ማመስገን እወዳለሁ ብለዋል።

የሳይንስ መሳሪያዎች ስልጠናና ምክር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንጂነር አበባየሁ ማሞ በበኩላቸው የክፍሉን ተግባራት ያብራሩ ሲሆን በዚህ መሰረት የሳይንስ መሳሪያ ተጠቃሚዎች ተግባሮቻቸውን በብቃት እንዲያከናውኑ ለማስቻል ከአቅማቸው በላይ ለሆኑ ሳይንስ መሳሪያዎች ተከላ፤ ኮሚሺኒንግ፤ ጥገናና ማስወገድ ስራዎችን በመስራት የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት እንዲሁም በህክምና መሳሪያዎች ተከላ፤ኮሚሺኒንግና ጥገና ስራ ለተሰማሩ ወርክሾፖች የብቃት ማረጋገጫ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ይህ ስልጠና በአናሎግና ድጂታል ኤሌክትሮኒክስ ላይ ትኩረት ያደረገ እና ለተከታታይ ሳምንታት በአራት ዙር ስድሳ ለሚሆኑ በከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ ስር ለሚገኙ የባዮሜዲካል ኢንጂነሮች እንደሚሰጥ ጠቁመው ተሳታፊዎች ስልጠናውን በትኩረት በመከታተል በቂ እውቀት መጨበጥ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የመድሀኒትና ሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦትና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰይፈ ደምሴ እንደተናገሩት ከዚህ በፊት በከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ ስር የሚገኙ የህክምና መሳሪያዎች አገልግሎት የሚሰጡት ከ50 በመቶ የማይበልጡ ነበሩ፡፡ ጤና ቢሮው ችግሩን በመረዳት ባከናወነው ጠንካራ ሥራ አሁን ላይ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑ የህክምና መሳሪያዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙና ይህ ባይሳካ ኖሮ ይወጣ የነበረውን ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስት ሀብት ማዳን መቻሉንም አስረድተዋል፡፡

አቶ ሰይፈ እንዳሉት ከኢንስቲትዩቱ ጋር ከረጅም ዓመታት አንስቶ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው ችግሮችን እንድንፈታ እና የተሟላ አገልግሎት በመስጠት የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልፀው ሠልጣኞችም ይህን እድል በአግባቡ በመጠቀም ከመሳሪያዎች ጥገና ባሻገር ወደፊት ለሚኖረን የቴክኖሎጂ ፈጠራ መዘጋጀት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም ዳይሬክተሩ ባለሙያዎቻችን ይህን ስልጠና እንዲወስዱ ለአማቻቹልን የኢንስቲትዩቱ አመራሮች ምሥጋና እናቀርባለን ብለዋል፡፡

Tags