themes/custom/conbiz የኢንስቲትዩቱ አመራሮችና ሠራተኞች በ2017 በጀት ዕቅድ እና በጊዜ አጠቃቀም ዙሪያ ውይይት አካሄዱ፡፡ | EMI Skip to main content
emi

የኢንስቲትዩቱ አመራሮችና ሠራተኞች በ2017 በጀት ዕቅድ እና በጊዜ አጠቃቀም ዙሪያ ውይይት አካሄዱ፡፡

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (ኢስኢ) የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሠራተኞች በ2017 በጀት ዕቅድ፣ በጊዜ አጠቃቀም፣ መልካም ሥነ-ምግባር እና ለጥናትና ምርምር የተቋሙን ነባራዊ ሁኔታ በማስመልከት በአዳማ ከተማ ውይይት አድርገዋል፤የአዳማ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪንም ጉብኝተዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቅረአብ ማርቆስ ከ2016-2017 ዓ.ም የተዘጋጀውን ስትራቴጂክ ዕቅድ መሰረት አድርገው ገለፃ አድርገዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ተቀዳሚ ተግባር ጥናትና ምርምር በማካሄድ ችግር ፈቺና ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን መሁኑን ያብራሩት አቶ ፍቅረአብ ለዚህም ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ዕቅዱ የተቋሙን አበይት ዋና ዋና ተግባራት ያካተተ ሲሆን በ2017 በጀት የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ ሁሉም የተቋሙ ሠራተኛ በኃላፊነት ስሜት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ ጨምረው አስገንዝበዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢንስቲትዩቱ የኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ አብርሐም የጊዜ አጠቃቀም፣ መልካም ሥነ-ምግባርና ለጥናትና ምርምር የኢንስቲትዩቱ ነባራዊ ሁኔታ ምን እንደሚመስል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም የራስን የኑሮ ሁኔታ ከማሻሻል ባለፈ ኢንስቲትዩቱ የተቋቋመበትን ዓላማና ተልዕኮ ለማሳካት እንደሚረዳ ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ አሰፋ ገለፃ እንደ ጊዜ አጠቃቀም ሁሉ የተሟላ ሰብዕና እና የተስተካከል ሥነ-ምግባር መላበስ ለራስ፣ ለቤተሰብና ለሀገር የሚኖረው ፈይዳ ከፍተኛ መሆኑን በተለይም ደግሞ እኛ የህዝብ አገልጋይ በመሆናችን መልካም ሥነ-ምግባር ተላብሶ ተገልጋይን ማርካት፤ ተቋሙንም አንድ እርምጃ ወደፊት ማራመድ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

መንግስት ለኢንስቲትዩቱ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት መሰረት ግዙፍ ህንፃዎች እየተገነቡ እና ህንፃዎችን የሚመጥኑ የላብራቶር መሳሪያዎች እየተገዙ በመሆናቸው ተቋሙ ለሚያደርጋቸው ጥናትና ምርምሮች መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም በፕርግራሙ ላይ ተገኝተው የማጠቀለያ እና የቀጣይ የስራ አቅጣጫ የሰጡት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ደርበው እንደተናገሩት ከዚህ በፊት እውቅና ካገኘንባቸው አራት የአለካ መስኮች በተጨማሪ በዚህ ዓመት በሙቀት አለካክ መስክ ሁለት ፓራሜትሮችን በዓለም አቀፍ የሥነ-ልክ ድርጅት የመረጃ ቋት BIPM-KCDB በማስመዝገብ ከአፍሪካ ዘጠነኛ ደረጃን በመያዛችን እንኳን ደስ አላችሁ፤ይህ ውጤት እንዲመጣ ለተጉ ባለሙያዎችም ምስጋና አቅርባለሁ ብለዋል፡፡ የአንድ ተቋም ራዕይና ተልዕኮ እውን የሚሆነው ዕቅድ በማቀድ ብቻ ሳይሆን እቅዱን መፈፀም የሚችል ብቁ የሰው ሀይል ማፍራት ሲቻል መሆኑን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህም በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡ ተቋሙ ካለበት ግዙፍ ሀገራዊ ኃላፊነት አኳያ ብዙ የቤት ስራ እንደሚጠብቀን በመገንዘብ በቀጣዩ በጀት ዓመት በሁሉም መስክ መሰረት የመጣል ስራ ይሰራል፤ ለዚህ ደግሞ ያለንን አቅም ሳንሰስት በአግባቡ መጠቀም ይኖርብናል ሲሉ በአፅንኦት አስገንዝበዋል፡፡

ከተሳታፊዎች መካል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት የቀረበውን ዕቅድ ውጤታማ ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ለተቋሙ ውጤታማነት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡