Skip to main content
emi

የሀገርን ምርት መጠቀም በራስ ከመተማመን ባለፈ የሀገርንም ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ተገለፀ፡፡

አዲስ አበባ፡ ነሀሴ 26/2017 ዓ.ም (ኢሥኢ) የኢትዮጵያን ይግዙ በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ከሚገኘው የንግድ ሳምንት ኤክስፖ አካል የሆነ የሃገር ውስጥ ንግድ ፓናል ውይይት በግዙፉ የጥራት መንደር ግቢ ውስጥ በኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት አዳራሽ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡ የፓናል ውይይቱን የከፈቱት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንደተናገሩት በ2017 ዓ.ም. በሃገር ውስጥ ንግድ ዘርፍ በሁሉም ረገድ የዕቅዳችንን መቶ ፕርሰንት በላይና ከቀደሙ ዘመናት አንጻርም ሲታይ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገብንበት ዓመት ቢሆንም ካለን እምቅ አቅም አንጻር ሲታይ ግን ገና ማከናወን የሚገቡ በርካታ ስራዎች እንዳሉ መገንዘብ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

እንደ ክቡር ሚኒስትሩ ገለፃ የኢትዮጵያን ይግዙ የሚለው መሪ ቃል ህብረተሰቡ ለሀገር ምርት ትኩረት እንዲሰጥና እንዲተማመን ብሎም ራሱን በመጥቀም የሀገርን ኢኮኖሚ እንዲያሳድግ ታስቦ ስለሆነ ይህን በመገንዘብ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊተገብረው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ይህ የንግድ ሳምንት በ2017 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ልምድ በመውሰድ ዘንድሮ ደረጃውን የጠበቀና ሁሉን ያሟላ ኢግዚቢሽን ማዘጋጀት እንደተቻለ ጨምረው አስረድተዋል፡፡

የፓናል ውየየቱን የመሩት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አብዱልሀኪም ሙሉ (ዶ/ር/ የኢትዮጵያን ይግዙ የሚለው መሪ ሀሳብ በጣም ጠጣርና ብዙ መስራት የሚጠይቅ ነገር ግን በራስ መተማመንን የሚፈጥር መፈክር ነው፡፡ የኢትዮጵያን ምርትና ሀሳብን እንዲገዙ ለዜጎች ተደራሽ የሆነ ብቻ ሳይሆን ጥራት ያለው ምርት ማቅረብ ግዴታ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አብዛኞቻችን ለሀገር ምርት ያለን አመለካከት የተዛባና እምነት ማጣት ከበፊት ጀምሮ ይዘነው የመጣን በመሆኑ ቶሎ ከጅግሩ ለመውጣት ሲከብደን ይስተዋል፡፡ይህን ችግር ለመቅረፍ በመንግስትም ሆነ በንግዱ ዘርፍ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም ከተወያዮቹ የተለያየ ሀሳቦችና ጥያቄዎች ተነስተው ከመድረክ አወያየች ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በፓናል ውይይቱ ላይ የመንግስት ተቋማት፣ የንግዱ ማህበረሰብና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡