themes/custom/conbiz የሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት ምርትና የኢኖቬሽን አውደ ርዕይ በሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡ | EMI Skip to main content
emi

የሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት ምርትና የኢኖቬሽን አውደ ርዕይ በሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20/2016 ዓ.ም (ኢስኢ) የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ከአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት እና ከሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት አምራች ማህበራት ጋር በመተባበር ከሰኔ 15-20/2016 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ አውደርዕይ በሚሊኒየም አዳራሽ እያካሄደ ይገኛል፡፡

በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰሩ ከሚገኙ ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው በተለያዩ ዘርፎች በአምራችነት የተሰማሩትን አገር በቀል አምራቾችን መደገፍና ማበረታታት ነው፡፡ ጤና ሚኒስቴርም ይህን ታሳቢ በማድረግ በዘርፉ የተሰማሩትን ማህበራት ለመደገፍ፣ ለማጠናከር፣ድርጅታቸውንና ምርታቸውን ለማስተዋወቅ፣ እንዲሁም እርስ በርስ የንግድ ትስስር ለመፍጠር የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አልፎም በዚህ ዘርፍ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማመላከት እንዲረዳቸው በማሰብ ይህን አውደ ርዕይ እንዲዘጋጅ ማድረጉን ከአስተባባሪዎቹ መረዳት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ከህክምና መሳሪያዎች ጋር ያለውን ከፍተኛ ቁርኝት በመገንዘብ ጤና ሚኒስቴር በአውደ ርዕዩ ላይ እንዲሳተፍ በሰጠው ዕድል መሰረት በሚሊኒየም አዳራሽ ተገኝቶ ተቋሙ የሚያከናውናቸውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት በገለፃ እንዲሁም የህክምና መሳሪያዎች በተግባር እንዴት ካሊብሬት እንደሚደረጉ አስተዋውቋል፡፡ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባና ሚኒስትር ድኤታዎች ተቋማችን ከጎበኙት መካከል ሲሆኑ ኢንስቲትዩቱ እያከናወነ ባለው ተግባር መደሰታቸውን ገልፀው ከዚህ የበለጠ መጠናከር እንዳለበትና ሚኒስቴር መስሪያቤቱም በቀጣይ ተቋሙን በተለያዩ ዘርፎች እንደሚደግፍ ተናግረዋል፡፡

አውደርዕዩ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣናት የጎበኙት ሲሆን ዛሬ ሰኔ 20/2016 ዓ.ም ከሠዓት በኋላ ፍፃሜውን ያገኛል፡፡