የኢንስቲትዩቱ አመራርና ሠራተኞች የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን ገመገሙ፡፡
የኢንስቲትዩቱ አመራርና ሠራተኞች የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን ገመገሙ፡፡
አዲስ አበባ፡ ሰኔ 22/2018 ዓ.ም (ኢ.ሥ.ኢ)
የኢትዮያ ሥነ-ልከ ኢንስቲትዩት አመራርና ሠራተኞች በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡
ሪፖርቱን ያቀረቡት የተቋሙ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ስንታየሁ ወንድሙ እንደገለፁት ሪፖርቱ የኢንስቲትዩቱን የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ፣ የሦስት ዓመት (2016-2018) የመካከለኛ ዘመን የልማት ዕቅድ እንዲሁም የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ተዋቅሮ የተዘጋጀ መሆኑን አውስተዋል፡፡
እንደ ሥራ አስፈፃሚዋ ማብራሪያ የተቋሙ የ2018 በጀት ዓመት ዋና ዋና ተግባራት አፈፃፀም 92 በመቶ ደርሷል፡፡ የደንበኞች ወይም የባለድርሻ አካላት እርካታን በማሳደግ ለገድ ከፍ ያለ አፈፃፀም የተመዘገበ ሲሆን በካሊብሬሽን አገልግሎት ዘርፍ ባለፈው ዓመት ከነበረበት 33 ሺህ 190 ወደ 35 ሺህ 19 በማሳደግ ከ10 በመቶ በላይ ብልጫ አሳይቷል፡፡ በሌላ በኩል የጥገና አገልግሎትን በተመለከተ የዘንድሮው አፈፃፀም ከ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር 73 በመቶ ብልጫ በማሳየት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ስንታየሁ አክለውም ከአፋር ክልል ሁሉም ዞኖች ለተወጣጡ የህጋዊ ሥነ-ልክ ባለሙያዎች እንዲሁም ከጂቡቲ ለመጡ ባለሙያዎች በህጋዊ ሥነ-ልክና በተተለያዩ የአለካክ መስኮች ላይ ስልጠና በመስጠት ዕቅዱን ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡ ተደራሽነትንና የበጀት አጠቃቀም ውጤታማነትን ከማሳደግ፣ የፋይናንስ ምንጮችን ከማበራከት፣ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትንና የአለካክ ወሰኖችን ከማሳደግ፣ የአሰራር ቅልጥፍናንና ቅንጅታዊ አሰራርን ከማሻሻል፣ የሠራተኛውን ብቃት ከማሳደግ ባሻገር የክትትልና ግምገማ ሥርዓትን ከማሻሻል አኳያ በዚህ በጀት ዓመት በርከት ያሉ መልካም አፈፃፀሞች መመዝገባቸውን ሥራ አስፈፃሚዋ አስረድተዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ሙሉጌታ ደርበው (ዶክተር) ውይይቱን ሲያጠቃልሉ እንደተናገሩት ያሳለፍነው የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን በብቃት ከመወጣት ባሻገር መደበኛ ሥራዎች ሳይንጠባጠቡ ጎን ለጎን ማስኬድ የቻልንበት፣ ከፍተኛ ርብርብ የተደረገበት፣ አብዛኛው ሠራተኛ መናበብ፣ መቀናጀትና ጠንከር ያለ የቡድን ሥራን ባህል ያደረገበት ዓመት በመሆኑ የተተቋማችን አፈፃፀም ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ በዚህ ዓመት የታየውን አፈፃፀም የበለጠ በማላቅ በቀጣዩ 2019 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን አህጉራዊ የአፍሪሜትስ ጉባኤ በላቀ ስኬት ለመወጣት የተጀመሩ የቅድመ-ዝግጅት ተግባራትንና፣ በተቋሙ የተጀመሩ የምርምር ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና ውጤታማነትን ለመጨመር የመንግሥት አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም ሥራዎችን በተሟላ መልኩ ማሳካት፣ የላቦራቶሪ መሣሪያዎችን ተከላ እና የኮሚሽኒንግ (Commissioning) ሥራዎችን በፍጥነት አጠናቆ መሣሪያዎቹን ሙሉ በሙሉ ወደ አገልግሎት ማስገባት ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም የሀገሪቱን ፍላጎት ለመመለስ የኬሚካል ሥነ-ልክ ላቦራቶሪዎችን የመለካት እና የሊብሬሽን አቅም ደረጃ በደረጃ ማሳደግ፤ የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ወቅታዊ ፍላጎት መሠረት በማድረግ ተቋሙ የሚሰጣቸውን የሥነ-ልክ አገልግሎት ወሰኖች (Calibration and Measurement Capabilities) በዓይነትና በደረጃ ማሳደግ ቀጣዩ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን በአፅንኦት አስገንዝበዋል፡፡
በመጨረሻም ያላቸውን አቅም ሳይሰስቱ ተጠቅመውና ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ለተቋሙ ስኬት የሚደክሙ ሰራተኞችን አመሰግነው ይህ የአንድነትና ስራን ባህል የማድረግ ልምድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስባለሁ ብለዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ
Facebook: http://www.facebook.com/emi.ethiopia
Website: www.ethiometrology.gov.et
Telegram: https://t.me/Ethiopian_Metrology_Institute
YouTube: https://www.youtube.com/@EthioMetrology
Email: info@ethiometrology.gov.et