Skip to main content
emi

ጥራትን ማስጠበቅ የሀገራችን ዋና ማጠንጠኛ ነጥብ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

አዲስ አበባ፡ ነሐሴ 27/12/2017 ዓ.ም (ኢሥኢ) የኢትዮጵያን ይግዙ በሚል መርህ ከተከፈተው የንግድ ሳምንት ጎን ለጎን ሁለተኛው ዙር የፓናል ውይይት ዛሬም በምርትና አገልግሎት ጥራት ማስጠበቅ ላይ ትኩረት በማድረግ በውቡ የጥራት መንደር ግቢ በኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

ፓናሉን በንግግር የከፈቱት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ካሣሁን ጎፌ /ዶክተር/ እንዳሉት የዛሬው ውይይት ዋና ዓላማ የተሰሩ ስራዎችን ለማውሳት ሳይሆን ከሰራነው ይልቅ ያልሰራነው ስለሚያመዝን የምርትና አገልግሎቶችን ጥራት እንዴት ማስጠበቅ እንደሚቻል ሀሳብ የሚመነጭበት፣ ችግሮች ተለይተው መፍትሄ የሚያገኙበትና ተግባራዊ ለማድረግ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መድረክ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ ክቡር ሚኒስትሩ ገለፃ ጥራትን የማስጠበቅ ጉዳይ ለአንድ ተቋም የሚተው ሳይሁን የሀገራችን ዋነኛ ማጠንጠኛ ነጥብ መሆኑን በመረዳት ርብርብ ማድረግ ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር ነው፡፡ ይህ ግዙፍ የጥራት መንደር ግንባታ መንግስት ለጥራት የሰጠውን ትኩረት በግልፅ የሚያመላክት ከመሆኑም ባሻገር የጎደሉ መሳሪያዎችን የማሟላትና በብቁ የሰው ሀይል የማደራጀት ተግባር በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የፓናል ውይይቱን የመሩት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ እንዳለው መኮንን እንደገለጹት አንድ ምርት ሲቀርብ ቅድሚያ የሚመጣው ጥያቄ ጥራቱን የጠበቀና ደነበኛን የሚያረካ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ ጥራትን ማስጠበቅ ዓለም አቀፉ የንግድ ስርዓት የሚፈልገው ዋና ጉዳይ መሆኑን ተገንዝበን የትኛውንም ስራ ስንሠራ ሁሌም ጥራትን እያሰብን መሆን አለበት ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በሌላ በኩል ጥራትን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የምርት አቅርቦትን ማሳደግ ብሎም የማይቆራረጥና ዝለቂነቱ ላይ ማተኮር ስንችል በዓለም የንግድ መድረክ ላይ በብቃት የመወዳደር ዕድል ይፈጥርልናል ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በማያቋርጥ የጋራ ጥረት የሀገራችንን ምርትና አገልግሎት እናሳድግ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፓናል ውይይቱ በከፍተኛ ምሁራን ታጅቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበትና ወደፊት ጥራትን ለማስጠበቅ ለሚከናወኑ ተግባራት አቅጣጫ የተቀመጠበት ሆኖ ተጠናቋል፡፡