በሁሉም ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
አዲስ አበባ፡ የካቲት 29/2017 ዓ.ም (ኢስኢ) የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ሰራተኞች በአለም ለ114ኛ በአገራችን ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ "ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል!" በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን /ማርች 8 በዛሬው ዕለት አክብረዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የሴቶች ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ተወካይ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ወ/ሮ ሮዛ ብርሃኑ ባደረጉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንደገለፁት በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መከበሩ እኩልነትን ቀስ በቀስ ባህል ለማድረግ እንደሚጠቅም ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ ሮዛ አክለውም ዓመት በመጣ ቁጥር ተሰባስቦ በዓሉን ማክበር ብቻውን በቂ ስላልሆነ በሁሉም ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቅረአብ ማርቆስ ፕሮግራሙን ሲከፍቱ እንዳሉት ሁሉን አቀፍ የሴቶች ተሳትፎ ሀገርን በመለወጥ ረገድ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት መድረኮች ግንዛቤን ከማሳደግ ባሻገር እርስ በርስ ለመተዋወቅና ትብብርን ለማጠናከር ብሎም የሴቶችን ተሳትፎና እኩልነት አጉልተን እንድናሳይ ይረዱናል ብለዋል፡፡
የሀሳብና የተግባር አንድነት በመፍጠር የተቋማችንን ተልዕኮ ማሳካትና ሀገርን መለወጥ ከሁላችንም ይጠበቃል ሲሉም አቶ ፍቅረአብ ጨምረው አስረድተዋል፡፡
በዕለቱ የእናት ጡት ጥቅም ለህፃናት በሲስተር ታሪክ አዳሙ እንዲሁም ሴቶችን በማብቃት ረገድ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ሚና ያለውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አስመልክተው አቶ አበባው ሰፋ ያለ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን በቀረቡት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነዶች ላይም ተሳታፊዎች ሞቅ ያለ ውይይት አድርገውባቸዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ስራ አመራር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽመልስ አበባው ውይይቱን ሲያጠቃልሉ እንደተናገሩት የሴቶች ተሳትፎና እኩልነት እውን የሚሆነው በጋራና በትብብር መንቀሳቀስ ሲችል ብቻ መሆኑን በመረዳት ሁሉም የስራ ክፍሎች ሴቶችን ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ ማዘጋጀትና መተግበር እንዳለባቸው አፅንኢት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቅረአብ ማርቆስ በበዓሉ ዙሪዯ ለተሳታፊዎች ያቀረቡትን ድንገተኛ ጥያቄ ለመለሱ ሦስት ሴቶች በግላቸው የገንዘብ ሽልማት አበርክተውላቸዋል፡፡