17ኛውን የአፍሪካ አህጉር የሥነ-ልክ ተቋም ስብሰባ የሚካፈል ልዑክ ወደ ኬንያ ማምራቱ ተገለፀ፡፡
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም (ኢስኢ) 17ኛውን የአፍሪካ አህጉር የሥነ-ልክ ተቋም ስብሰባ ለመካፈል በኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቅረዓብ ማርቆስ የተመራ ልዑክ በዛሬው እለት ከአቻ የሥነ-ልክ ተቋም አመራሮች እና ቴክኒካል ኮሚቴዎች ጋር በጋራ እና በአህጉር አቀፍ የሥነ-ልክ ጉዳዮች ላይ በናይሮቢ ኬንያ ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛል።
ም/ዋና ዳይሬክተሩ ከቦታው ባደረሱን መረጃ እንደገለፁት እየተካሄደ ያለው ጉባኤ ጠቀሜታ ከውይይት በላይ ሲሆን በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የልኬትን እና የመለኪያ መሳሪያዎች ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ በሚደረግ ሥነ-ልካዊ የፅንሰ ሀሳብ እና የተግባር አንድነት ላይ የልምድ ልውውጥ ለማምጣት ያስችላል። ወይይቱ በኢትዮጵያ የስነ-ልክ ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ እና በሀገሪቱ ውስጥ የላቁ የመለኪያ ስርዓቶችን ለማጎልበት እንደሚያስችል እምነት እንደተጣለበት ተናግረዋል። ይህ መድረክ ትብብርን በማጎልበት እና በሥነ-ልክ ጉዳዮች ላይ እውቀትን በማካፈል፣ የፈጠራ ሀሳቦች እና ምርጥ ልምዶች መለዋወጫ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሥነ-ልክ ደረጃ ለማሻሻልም ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡001
እንደ አቶ ፍቅረአብ ማብራሪያ መድረኩ በሥነ-ልክ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት መካከል የእውቀት መጋራት፣ የሃሳብ ልውውጥ እና ትብብርን ያመቻቻል። ከአቅም ግንባታ አንፃር ደግሞ የሥነ-ልክ ባለሙያዎችን ክህሎት እና እውቀት ለማሳደግ፣ ወርክሾፖች እና የስልጠና ክፍለ ጊዜዎች ሊመቻቹ የሚችሉበትን ስልት የመፍጠር፣ የሁለትዮሽ እና አህጉር አቀፍ የመለኪያ እስታንዳርዶች የንፅፅር ፐሮግራሞች እንዲኖሩ ማድረግ፣ ቀጣይነት ያለው የእርከን ተዋረድ ትስስር ማስጠበቅ የሚቻልበትን መንገድ ለማመቻቸት እንዲሁም የአለካክ ስርዓትና የልኬት ደረጃዎችን በማስማማት የመለኪያዎችን ወጥነት እና ንፅፅር እንዲረጋገጥ በማድረግ ረገድ ውይይቱ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመው ጥራት ያለው መሠረተ ልማት ከመፍጠር አንፃር ደግሞ ለኢንዱስትሪና ለንግድ ድጋፍ የሚሆኑ ብሔራዊ የሥነ-ልክ ተቋማት፣ የካሊብሬሽን ላቦራቶሪዎች እና የሪጉላቶሪ ቁጥጥር አካላት እንዲጠናከሩ የሚያበረታታ መሆኑንም ጨምረው ገልፃዋል።