themes/custom/conbiz ኢንስቲትዩቱ “ለተሻለ ነገ ዛሬ እንለካለን” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፉን የሥነ-ልክ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች አከበረ፡፡ | EMI Skip to main content
world metrology day

ኢንስቲትዩቱ “ለተሻለ ነገ ዛሬ እንለካለን” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፉን የሥነ-ልክ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች አከበረ፡፡

ኢንስቲትዩቱ “ለተሻለ ነገ ዛሬ እንለካለን” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፉን የሥነ-ልክ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች አከበረ፡፡

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2016 ዓ.ም (ኢስኢ) የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሠራተኞች ዓለም አቀፉን የሥነ-ልክ ቀን “ለተሻለ ነገ ዛሬ እንለካለን” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ባዘጋጀው ወርክሾፕ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ደርበው እንደገለፁት የዓለም የሥነ-ልክ ቀን እ.ኤ.አ ግንቦት 20/1875 በአስራ ሰባት ሀገራት ተወካዮች የተፈረመው የሜትር ስምምነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወስበት በዓል ነው፡፡ እ.ኤ.አ መስከረም 2023 በወጣው ሪፖርት መሰረት የአባል ሀገራት ቁጥር 64 የደረሰ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ 33 ሀገራት ተባባሪ አባል መሆናቸውን ጠቁመው ስምምነቱ ዓለማችን ሳይንሳዊ መሰረት ያለው ተናባቢ፣ ተሳሳሪና ተመሳሳይ አሃድ መጠቀም እንድትችል እድሉን የከፈተና ለኢንዱስትሪ፣ ለንግድና ለማህበረሰብ ልማት ዓለም አቀፍ የትብብር ማዕቀፍ የጣለ እና የስምምነቱ ዓላማ ዛሬም ድረስ የ1875ቱን ያክል የዓለማችን አስፈላጊ አጀንዳ በመሆን የቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ኢንስቲትዩታችንም ለሀገራችን ብልፅግና የሚኖረውን አበርክቶት ለማሳደግ፣ አገልግሎታችንን ለማሻሻል፣ የአሰራር ክህሎታችንን፣ ብቃታችንን ለመገንባት ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት እድል ይፈጥርልን ዘንድ በርካታ ጥረቶች በማድረግ የሥነ-ልክ ቀንን በየዓመቱ እያከበረ ይገኛል፡፡ በዓሉ ለኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች፣ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች በስነ-ምግባራቸውና ቅን ልቦናቸው፣ በጽሁፎቻቸውና በውጤታማ አፈፃፀማቸው እውቅና እና ሽልማት የሚሰጥበት እንዲሁም የተቋሙ ማህበረሰብ በጋራ ማዕድ እየተካፈለ ለቀጣይ ስራ ራሱን የሚያድስበት ዕለት ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም በዓሉ ሀላፊነታችንን የበለጠ የምንወጣበት የተሻለ መነሳሳትና ግንዛቤ ለመፍጠር እድል የሰጠ መሆኑን ገልፀው ቀኑን በስኬት እንድናከብር ድጋፍ ያደረጉ የኢንስቲትዩታችን አገልግሎት ተጠቃሚዎችን፣የልማት አጋሮቻችን እና ባለድርሻ አካላትን ከልብ አመሰግናለሁ ያሉ ሲሆን ለበዓሉ የዝግጅት ኮሚቴ እና በቅንነት ስራውን ለተባበሩ የተቋሙ ሠራተኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በወርክሾፑ ላይ የተቋሙን አጠቃላይ ገፅታ የሚዳስስ ፅሁፍ በኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በአቶ ፍቅረአብ ማርቆስ እንዲሁም ዓለም አቀፉን የሥነ-ልክ ቀን በተመለከተ ደግሞ የኢንስቲትዩቱ የሳይንሳዊ ሥነ-ልክ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ጌርጊሶ አቅርበዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገመቹ አመንቴ የተቋሙን የካሊብሬሽን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን እንዲሁም የካሊብሬሽን አገልግሎት አሰጣጥን በከፊል ለማዘመን የሚረዳ ሲስተምን የተመለከተን ጉዳይ ደግሞ አቶ አየነው ጌታነህ አስተዋውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በUSAID USP ፕሮግራም ከፍተኛ የቴክኒክ ባለሙያ የሆኑት አቶ ወንደሰን ፍስሃ እንዲሁም በኢትዮጵያ የ PTB ፕሮጅክት አስተባባሪ አቶ ካሰኝ ከበደ ድርጆቶቻቸውን ያስተዋወቁ ሲሆን ከተቋማችን ጋር በአጋርነት እንደሚቀጥሉም ቃል ገብተዋል፡፡

በመጨረሻም ከበዓሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሦስት ጥናታዊ ፅሁፎች በኢንጂነር ትርፌሳ ባይሳ፣ በአቶ ፀደቀ ብርሐኑ እና በአቶ አንዳርጌ በለጠ በአውደ-ጥናቱ ላይ ቀርበው በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ለፅሁፍ አቅራቢዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቶ አውደ ጥናቱ ተጠናቋል፡፡ በተጨማሪም ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለተቋሙ ሠራተኞች እና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች የምሳና የመዝናኛ ሮግራም በማዘጋጀት በዓሉ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡