Skip to main content
emi

ኢንስቲትዩቱ ለግንባር ቀደም ሠራተኞች የዕውቅናና ሽልማት ሥነ-ስርዓት አካሄደ፡፡

የኢትዮጵያን ይግዙ በሚል መሪ ቃል ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከነሐሴ 19-23/2016 ዓ.ም ያዘጋጀውን የንግድ ሳምንት ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት በ2016 በጀት ዓመት የጎላ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ምስጉን ሠራተኞች የዕውቅናና ሽልማት ሥነ-ስርዓት አካሂዷል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙትና ለግንባር ቀደም ሠራተኞች ሽልማቱን የሰጡት የንግድና ቀጣናዊ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክቡር አቶ እንዳለው መኮንን እንደተናገሩት የሀገር ገቢን ለማሻሻል የወጪ ንግድ ጥራትን ማስጠበቅና የሀገር ውስጥ ምርት የመግዛት ባህልን ማሳደግ ወሳኝ ነው፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በዚህ ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ሰሞኑን እየተካሄደ የሚገኘው የንግድ ሳምንት ማረጋገጫ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ሚንስትር ዴኤታው ገለፃ የዚሁ የንግድ ሳምንት አካል የሆነውና ሚንስቴር መ/ቤቱና ተጠሪ ተቋማት በየዘርፋቸው የተሻለ አፈፃፀም ያላቸውን ሠራተኞች ለማበረታታት ዕውቅና እየሰጡ ይገኛሉ፤በዚህ መሰረት ዛሬ ዕውቅናና ሽላማት ያገኛችሁ በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ከዚህ በፊት ባለሙያዎችን ለስልጠና፣ ለካሊብሬሽን ስራና ተያያዥ ጉዳዮች አፍሪካ ውስጥ ወደሚገኙ የሥነ-ልክ ተቋማት በመላክ ስራ ያሰራ ነበር፡፡ እየተገነቡ የሚገኙት ግዙፍ ህንፃዎች ሲጠናቀቁ ይህ ተቋም የአፍሪካ የሥነ-ልክ ማዕከል በመሆን ባለሙያዎች ከዚህ እየተነሱ ስራ የሚሰሩበት፣ ሀሳባቸውን የሚሸጡበት፣ የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርጉበት፣ ስልጠና የሚሰጡበትና የትሬሴብሊቴ ማዕከል የሚሆንበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም፤ለዚህ ደግሞ ከዚህ በበለጠ በርትቶ መስራት ይጠይቃል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉጌታ ደርበው የዕውቅናና ሽልማት ሂደቱን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ለራሳቸው ሳይሰስቱ ሙሉ አቅማቸውንና ጊዜያቸውን ተጠቅመው ለሰሩ ምስጉን ሠራተኞች ዕውቅና መስጠት ተገቢ ነው፡፡ በተቻለ መንገድ አሳታፊና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ምልመላ በማድረግ የጎላ ሚና የነበራቸውን ፈፃሚዎች ለመለየት ጥረት ተደርጓል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በቀጣይ ከዚህ ተሞክሮ በመውሰድ ከዚህ የተሻለ መስፈርት በማውጣት ግንባር ቀደሞችን የመሸለም ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡ ተሸላሚዎች በቀጣይ የበለጠ የምትሰሩበት ያልተሸለማችሁ ደግሞ ሙሉ አቅማችሁን ስራ ላይ በማዋል የተቋሙን ተልዕኮ ከማሳካት ባሻገር ለሽልማት መዘጋጀት ይኖርባችኋል ብለዋል፡፡

ከተሸላሚዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ሽልማቱ የበለጠ አቅምና መነሳሳትን የሚፈጥር በመሆኑ ለወደፊትም ከዚህ የተሻለ ለመስራት ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሰጡት አስጠያየት እንደገለፁት ተቋሙ ግንባር ቀደሞችን ለይቶ እውቅና መስጠቱ አስደስቶናል እኛም እንደ እነርሱ ተግተን በመስራት ተሸላሚ እንደምንሆን እርግጠኞች ነን ብለዋል፡፡

ዕውቅናና ሽልማት ያገኙት አስራ ዘጠኝ ሠራተኞች ሲሆኑ እንደየደረጃው ከከፍተኛው 30 ሺህ ብር እስከ ዝቅተኛው 6 ሺህ ብር ድረስ የተሸለሙ ሲሆን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉጌታ ደርበው ከተከታይ አመራሮቻቸው ጋር በመሆን ላሳዩት የአመራር ብቃት ከሠራተኞ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡