ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው::
መድረኩን በንግግር የከፈቱትና የእንኳን ደህና መጣችሁ መልክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉጌታ ደርበው እንዳሉት “ስልጠና ስልጡን እንሆን ዘንድ መልካም ነው” ልንሰለጥን ተገናኝተናል። በዚህም ያለንን አዋጥተን፣ ደምርን እንዲሁም ተባብርን በመስራት እራሳችንን፣ ተቋማችንን ብሎም ሀገራችንን ለመገንባት በሚረዳ መንፈስ ላይ በመሆን በአትኩሮትና በልበ ሙሉነት ስልጠናችንን እንድንከታተል እጠይቃለሁ።
ዶ/ር ሙሉጌታ ደርበው ቀጥለው እንዳሉት ሀገራችን ከርሃቡ፣ ከጥሙ፣ ከመልካም አስተዳደር እጦቱና አጠቃላይ እንግልቱ እንዲሁም በዘመናት መካከል ከተጫኑባት ሌሎች ስቃዮች/ጉስቁልናዎች ሁሉ በላይ የሀገሩን ህልውናና እንድነቱን የሚያስቀድም፣ ሀገረ መንግስት ወዳድና አክባሪ ፣ ለወገኑ መኖር መስዋት መሆንን የተካነ ህዝብ ባለቤት ነች። ይሁንና በሀገራችን ተፈጥሮ ሐብቶች እና በወገን ወዳድ ቅን ህዝቦቿ የሚቀኑ የቅርብ እና የሩቅ ጠላቶች ከረጅም ዘመን አንስቶ ባላቸው አቅም ሁሉ ሊጎዷት ሲሞክሩ ቆይተዋል።
እነኝህ ጠላቶች ተግተው በሚያፈራርቁብን ፈተናዎች መሃል የሀገራችንን ክብር እና ሉአላዊነት ማስቀጠል ተችሏል:: አለምን አስደማሚ የሆኑ የልማት ስኬቶች ማስመዝገብ ተችሏል። ስለሆነም እየገጠሙን ባሉ ፈተናዎች ተስፋ ሳንቆርጥ ሀገርን ለማበልጸግና ለማጽናት እንድንችል የምንሰለጠንበት እና የምንወያይበት ይህ መድረክ እንደሚያስፈልግ በመንግስት ታምኖ ወይይቶች እየተደረጉ ሲሆን፤ የዚሁ አካል የሆነው ከእዳ ወደ ምንዳ ሰልጠና በኢንስቲትዩታችን ዛሬ ተጀምሯል፤ በነገው እለትም የሚቀጥል ይሆናል። ስለዚህ የስልጠናውን ዓላማ በሚመጥን ተነሳሽነት ስልጠናውን እንድትከታተሉና እንድትሳተፉ አሳስባለሁ ብለዋል።
በሰልጠናው መክፈቻ ስነ ስርዓት ብሄራዊ መዝሙራችን በድምቀት ተዘምሯል። በተጨማሪም መክፈቻ ሥነሥርዓቱ በዳቦ ቆረሳ እና ቡና ስነ -ሥርዓት፣ “ስልጠና ይጥቀመን” በሚል ስሜት ቀስቃሽ ግጥም፣ በዲጄ በተመረጡ ልዩ ልዩ የብሄር ብሄረሰቦች ሙዚቃዎች እንዲደምቅ ሆኗል።