Skip to main content
emi

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌ በዘጠኝ ወሩ ከፍተኛ አፈፃፀም መመዝገቡን ገለፁ፡፡

አዲስ አበባ፡ ሚያዝያ፡ 1/2017 ዓ.ም (ኢሥኢ)

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት "ቀጣናዊ ትስስርና ዓለማቀፋዊ ተወዳዳሪነት ለንግድ ዘርፍ እድገት!" በሚል መሪ ቃል የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ተካሂዷል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌ እንደገለፁት ለሀገር ውስጥ ንግድ በተሰጠው ትኩረት ነባር ቅዳሜና እሁድ የገበያ ማዕከላትን ከማጠናከር ባሻገር በሀገር አቀፍ ደረጃ 3 መቶ 74 አዳዲስ ማዕከላትን በመገንባት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡ የስሚንቶ ዋጋን በእጥፍ እንዲቀንስ በማድረግ እንዲሁም ከዚህ በፊት በአንድ በተወሰነ አካል ይዘወር የነበረውን የጨው ግብይትን ስርዓት እንዲይዝ በማድረግ አበረታች ስራ መስራት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

እንደ ክቡር ሚኒስትሩ ማብራሪያ በወጪ ንግድ ዘርፉም የታየው አፈፃፀም ከፍተኛ ሲሆን ኢትዮጵያን በ2018 ዓ.ም የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ የተጠሪ ተቋማት የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም የሚያበረታታ ነው ያሉት ዶክተር ካሳሁን በቀሪዎቹ ሦስት ወራት በእጥረት የታዩ ተግባራትን የማካካሻ ዕቅድ በማውጣት ማከናወን ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን በዚህ ዘጠኝ ወር የላቀ አፈፃፀም መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡

በወይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ደርበው የተቋማቸውን የዘጠኝ ወር አፈፃፀም አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ሚኒስትር ዴኤታዎች፣የሚኒስትር መስሪያቤቱ የስራ ኃላፊዎችና የተጠሪ ተቋማት ዋና ዳይሬክተሮች ሪፖርታቸውን አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ከግምገማው መተናቀቅ በኋላ ክቡር ሚኒስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌና ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም የሚኒስቴር መስሪያቤቱ የስራ ኃላፊዎች የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ያዘጋጀውን የፎቶ አውደ ርዕይ ጎብኝተዋል፡፡