Skip to main content
emi

በአናሎግና ድጂታል ኤሌክትሮኒክስ ዙሪያ ሲሰጥ የነበረው ሁለተኛው ዙር ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡

አዲስ አበባ፣ የካቲት 08/2016 ዓ.ም (ኢስኢ) በኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩትና በአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ትብብር የተዘጋጀውና በሳይንስ መሳሪያዎች ስልጠናና ምክር ዳይሬክቶሬት በአናሎግና ድጂታል ኤሌክትሮኒክስ ዙሪያ ሲሰጥ የነበረው ሁለተኛው ዙር ስልጠና ተጠናቋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው የምስክር ወረቀት የሰጡትና ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቅረአብ ማርቆስ እንዳሉት ለተከታታይ 15 ቀናት ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና በብቃት ተወጥታችሁ ለዚህ ስለበቃችሁ እንኳን ደስአላችሁ ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ፍቅረአብ ገለፃ በሀገር ግንባታ ውስጥ ብቁ የሰው ሀይል ማፍራት መሰረታዊ ተግባር በመሆኑ እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች አስፈላጊ ናቸው፡፡ በሀገራችን ባሉ የጤና ተቋማት የሚገኙ የህክምና መሳሪያዎች ለበርካት የህብረተሰብ ክፍል አገልግሎት መስጠት እያቻሉ በቀላል ችግር ምክንያት ምንም ስራ ሳይሰሩ ለብልሽት የሚዳረጉበት አጋጣሚ ብዙ በመሆኑ የወሰዳችሁት ስልጠና ይህን ችግር በመቅረፍ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ም/ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም እናንተ ወጣቶች እንደመሆናችሁ ከፊት ለፊታችሁ ብዙ ነገር ስለሚጠብቃችሁ ልምድ ካላቸው መሀንዲሶች እውቀት መቅሰማችሁ ትልቅ ዕድል መሆኑን ጠቅሰው ያገኛችሁትን እውቀት ወደተግባር በመቀየር ሀገራዊ ግዴታችሁን ልትወጡ ይገባል፡፡ በሄዳችሁበት ሁሉ የተቋማችን አምባሳደሮች እንደምትሆኑና አብረን እንደምንሰራ ተስፋዬ የፀና ነው ሲሉም ጨምረው ገልፃዋል፡፡

የሳይንስ መሳሪያዎች ስልጠናና ምክር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንጂነር አበባየሁ ማሞ በበኩላቸው ሰልጣኞች በስልጠና ወቅት ለነበራቸው መልካም ስነ-ምግባር እና ንቁ ተሳትፎ እንዲሁም ስልጠናው በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ የዳይሬክቶሬቱ ባለሙያዎች ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

ሰልጣኞች ስልጠናውን ከመውሰዳቸው በፊት በተዘጋጀ የመግቢያ ፈተና አጠቃላይ ውጤታቸው 37 ከመቶ የነበረ ሲሆን ስልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ ግን 84 ከመቶ ማምጣታቸው በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተገልጧል፡፡

ከሰልጣኞቹ መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ንድፈ-ሀሳብን ከተግባር ጋር አዋህደው ለሰጡን ትሁትና ብቁ አሰልጣኞች ምስጋና ይገባቸዋል ካሉ በኋላ በቀጣይ ስልጠናው በማንዋል ቢታገዝ እና የተማሉ ማሽኖች ቢኖሩት የበለጠ ውጤታማ መሆን ይቻላል ሲሉ የጠቆሙ ሲሆን ለጥያቄዎቹ ከመድረክ ምላሽ እና የምስክር ወረቀት በመስጠት ተጠናቋል፡፡