themes/custom/conbiz በቂ ክህሎትና መልካም ስነ-ምግባር ያለው ባለሙያ ለማፍራት የተቋም ባህልና የሠራተኞች ባህሪ ግንባታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ተጠቆመ፡፡ | EMI Skip to main content
emi

በቂ ክህሎትና መልካም ስነ-ምግባር ያለው ባለሙያ ለማፍራት የተቋም ባህልና የሠራተኞች ባህሪ ግንባታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ተጠቆመ፡፡

አዲስ አበባ፡ ሚያዝያ 07/2016 ዓ.ም /ኢስኢ/ በስነ-ምግባራዊ አመራር፣ በካሊብሬሽን አገልግሎት አሰጣጥ፣ በትራንስፖርት ስምሪት መመሪያ እንዲሁም በስነ-ምግባር ኮድ መመሪያ ዙሪያ የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት የሥራ ኃላፊዎች የተሳተፉበት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ደርበው መድረኩን ሲከፍቱ እንደተናገሩት በቂ ክህሎትና መልካም ስነ-ምግባር ያለው ባለሙያ ለማፍራት የተቋም ባህልና የሠራተኞች ባህሪ ግንባታ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አንዱ ማሳያ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክሩ ለአብነት ከዚህ በፊት በውስጥ አቅም የተሰጡ የስነ-ምግባር ግንባታ ስልጠናዎች፤ የተቋም ባህል፣ የጊዜ አጠቃቀም ክህሎት ግንባታ ስልጠናዎች፣ እንዲሁም በስራቸው ጎልተው የሚታዩ መልካም አፈፃፀም ያላቸው ሠራተኞችን ያከበረና ያስቀደመ አሰራር ለማስፈን ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑ የሚጠቀስ ነው፡፡ በቂ ክህሎትና የተደራጀ የሰው ሀይል ማፍራት እንደተጠበቀ ሆኖ በጋራ መቆምና ለአንድ ዓላማ ተባብሮ መስራት ደግሞ ውጤታማ ተቋም ለመገንባት ወሳኝ በመሆኑ በዚሁ መሰረት መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የስነ-ምባር መከታተያ ክፍል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሠፋ ተስፋዬ ስነ-ምግባራዊ አመራር በሚል ርዕስ ስልጠና የሰጡ ሲሆን በመርሆዎች፣ እሴቶች፣ የስነ-ምግባር አስፈላጊነት፣ መገለጫዎችና መሰል ነጥቦች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩል በኢንዱስትሪያል ስነ-ልክ ዳይሬክቶሬት የካሊብሬሽን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የታዩ ክፍተቶችን አስመልክቶ የተዘጋጀውን የዳሰሳ ጥናት በኢንስቲትዩቱ የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ዳይሬክቶሬት የፀረ-ሙስና መኮንን በሆኑት በአቶ ወሠኔ መንገሻ ቀርቧል፡፡ የካሊብሬሽን አገልግሎት አሰጣጥ የአሰራር ስርዓት የመንግስት ህግና ደንብን ተከትሎ መሰጠት አለመሰጠቱን ዓላማ ያደረገ ሲሆን በቀረበው ጥናት ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቀጠሮ ያለማክበር፣ ማጓተት፣ ተገቢ ምላሽ አለመስጠት፣ የአቅም ማነስ፣ የተጠያቂነት አለመኖር፣ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት ተደራሽ አለመሆን በአጠቃላይ 50 በመቶ የሚሆነው በክፈተት የሚታይ መሆኑን በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

የትራንስፖርት ስምሪት የአሰራር ግልፀኝነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የትራንስፖርት ስምሪት መመሪያ ቁጥር 32/2004 አስመልክቶ የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ የኦዲት ባለሙያ አቶ ክንፈ ብርሐነ እንዲሁም የኃላፊዎችና ሠራተኞች የስነ-ምግባር መመሪያ ኮድ 1/2015 ደግሞ የሙስና መረጃ አስተዳደርና ትንተና ባለሙያ በሆኑት በወ/ሮ ንብረት ኡስማን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ይህ መድረክ ተቋማችን ያለበትን ቁመና ከሞላ ጎደል የተገነዘብንበት ከመሆኑም በላይ እኛ በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለብን ራሳችንን የፈተሽንበትና የቤት ስራ የወሰድንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎች አያይዘውም ጥንካሬዎችን የበለጠ ለማስቀጠል፣ ክፍተቶችን ደግሞ ፈጥኖ ለማረም በስራችን ያሉ ሰራተኞችን አቅም በመገንባት የኢንስቲትዩቱን ተልዕኮ ለማሳካት የአመራርነት ሚናችን እንወጣለን ብለዋል፡፡