themes/custom/conbiz አንድመቶ ሃያስምንተኛው የአድዋ ድል በዓል በኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ተከበረ፡፡ | EMI Skip to main content
Adwa

አንድመቶ ሃያስምንተኛው የአድዋ ድል በዓል በኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ተከበረ፡፡

ዓርብ የካቲት 22/2016ዓ.ም ኢሥኢ ጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች(አባቶቻችን) የዛሬ አንድመቶ ሃያ ስምንት ዓመት በአድዋ ተራሮች ተዋግተው በትዕቢት፣በጉራና በእብሪት ተወጥሮ የመጣን የነጭ አክራሪ ኃይል አይቀጡ በመቅጣት የዓለምን የፖሊቲካ ታሪክ ለዘላለም የቀየረ ድል ያበሰሩበትን ዕለት የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ሰራተኞች ሐሙስ የካቲት 21/2016ዓም በመድረክ ውይይት አክበረውታል፡፡

በውይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉጌታ ደርበው እንዳሉት ከመቶ ሃያ ስምንት ዓመታት በፊት የካቲት 23 ቀን ከመላው ኢትዮጵያ በከተቱ ፆታ፣እምነት፣ብሄር፣ የኑሮና የግንዛቤ ደረጃ ያልገደባቸው ገበሬዎች፣ አርብቶ አደሮች፣ ነዋሪዎች፣ ከተለያየ የሕብረተሰብ ክፍል የተሰባሰቡ ተዋጊ ዘማቾች የራሳቸውን ስንቅና ትጥቅ በግል ይዘው፤ ትጥቅና ስንቁ በዘመናዊ መንገድ ተሟልቶለት የመጣን የጣሊያን ወራሪ ኃይል በአድዋ ድል አድርገዋል፡፡ ይህ ድል የሰው ልጅ ነኝ የሚል በሌላው ላይ ሊያደርስ የማይገባው እንግልትና መከራ ለወረደባቸው እንዲሁም ላንገሸገሻቸው በመላው ዓለም ለሚገኙና ለአፍሪካ ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ፋናን የለኮሰ ሀገራችን ኢትዮጵያንም የተጋድሎ አርማቸው አድርገው እንዲወስዱ ያደረገ ክስተት ከመሆኑ በተጨማሪ በወራሪው የጣሊያን መንግስት ላይ የአስተዳደር ለውጥ እንዲመጣም አስገድዷል፡፡

ዶ/ር ሙሉጌታ ጨምረው እንዳሉት ይህ ድል አሁን ያለነው ዜጎች ቆራጦች ከሆንን፣ ጠንካራ ዓላማ ካለን፣ አንድነታችንን አጽንተን መጓዝ ከቻልን የትኛውንም አይነት ችግርና ጨለማ ማለፍ እንድንችል የሚረዳ የሕይወት ዘመን ብርሃን ነው ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለው እንዳሉት ለታሪክና ለታሪክ አስቀጣዩ ሕዝብ ክብር በመስጠት የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለገነባው የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍ ያለምስጋዬን አቅርባለሁ እንዲሁም በዓሉ በመከላከያ ሠራዊቱ አስተባባሪነት መከበሩ የባለቤትነት ክብርና ተጨባጭነት ያለው ፋይዳ እንዲኖረው ያስችላል ብዬም አምናለሁ ብለዋል፡፡

በመጨረሻ እንደተናገሩት ሁላችንም በተሰማራንበት ቦታ ሁሉ በታማኝነት፣በቅንነትና በትጋት ኃላፊነታችንን ከተወጣን ከታነጽንባቸው እንደ አደዋ ያሉ የማንነት ምሰሶዎች ጋር ራስን የማዛመድ ያክል ዋጋ ያለው ኩራትና ክብር ባለቤት እንሆናለን ብለዋል፡፡

ከዋና ዳይሬክተሩ የመክፈቻ ንግግር በኋላ በመከላከያ ሠራዊቱ የተዘጋጀውን የመወያያ ሰነድ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቅረዓብ ማርቆስ ያቀረቡ ሲሆን ከዋናዋና ሃሳቦች መካከል አያቶቻችን የዛሬ አንድመቶ ሃያ ስምንት ዓመት በብሔራዊ የአርበኝነት ስሜት የማይቻል የሚመስለውን በመቻል የተቀዳጁት አንፀባራቂ ድል ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ችቦና አርማ በመሆን ከአውሮፓዊያን ቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡ ስለማስቻሉ፤ ይኽው በዓል ለመቶያ ሰባት ዓመታት በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ የመጣ ሲሆን

ከ 2015ዓ.ም በኋላ ጀምሮ በዋናነት የኢፌድሪ መከላከያ ሚኒስቴር እያስተባበረው እንዲከበር በተወሰነው መሰረት በዓሉን በሚመጥኑ መርሃ ግብሮች በድምቀት እየተከበረ ስለመገኘቱ፤ የዓድዋ ድል የራሱ የሆነ ቋሚ መታሰቢያ ያልነበረወ ቢሆንም ዘንድሮ ለድሉ የሚመጥን የዓድዋ ድል መታሰቢያ በመገንባት አንድ መቶ ሃያ ስምንተኛውን የዓድዋ ድል በዓል “አድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል!” በሚል መሪ ቃል በልዩ ሁነትና ድምቀት እየተከበረ ስለመገኘቱ፤ ሠራዊታችን ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት፣ ለሕዝቦቿ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም ለሀገረመንግሥት መጽናትና የግዛት አንድነት መከበር በታላቁ የዓድዋ ድል የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና የቀን ሐሩር እና የሌት ቁር ሳይበግረው የአካልና የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ኢትዮጵያ ሀገራችን ወደ ከፍታ ማማ እንድትገሰግስ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ስለመገኘቱ በንባብ አሰምተዋል፡፡ በተጨማሪም የዓድዋ ድል የህብረብሔራዊነት መገለጫና የጥቁር ሕዝቦች ከፍታ ስለመሆኑ፤ በዓድዋ እሴቶች ድል እያስመዘገበ ሀገር ያፀና ትውልድ ስለመፈጠሩ ከነመገለጫዎቹ፤ ሠራዊታችን በዓድዋ እሴቶች ፈተናዎችን እየተሻገረ ሀገራዊ ክብርን ስለማስቀጠሉ ዘርዘር ያሉ ሃሳቦችን በንባብና በሰፊው አቅርበዋል፡፡

ከሰነዱ መቅረብ በኋላ በዶክተር ሙሉጌታ አወያይነት ሰራተኞች የተሳተፉበት የውይይት ጊዜ የነበረ ሲሆን በዛ ያሉ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ መድረኩ እንደአጠቃላይ ግጥም የቀረበበትና የሻይ ቡና ሴረሞኒም የታከለበት ደማቅ ቆይታ ነበር፡፡